በድሬዳዋ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የሰላም መደፍረስ በኢትዮጵያውያን ባህላዊ የእርቅ ስርዓት እልባት ለመስጠት የሚያስችል የሰላም ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው፡፡
ነሃሴ 04 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚካሄደው ፌስቲቫሉ በድሬዳዋ ተወላጆች የተዘጋጀ ሲሆን ባህላዊ የዛፍ ስር እርቅ ስነስርዓት የሚደረግበት መሆኑንም አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ የርካታ እሴቶች ባለቤት፣ ከህዝቦቷም አልፎ ለዓለም የሚበቃም የቱባ ባህል ባለቤት ሃገር ናት፡፡ ባህላዊ የሽምግልና ስነስርዓት ደግሞ ከነዚህ ቱባ እሴቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሽምግልና ባህል እንደየህዝቦቷ አከባቢያዊ ወግ ቢለያይም ፍትህን በመስጠት ግን ከሳይንሳዊው የዘመናዊው የፍርድ ቤቶች ሂደትም ተፎካካሪ መሆኑን በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡
በድረዳዋ ያለ፣ ለዘመናት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረም፤ የተኮራረፈን በፍጹም ይቅርታ የሚያስታርቁበት “muka jala” ወይም “Geed Hoost” የሚሉት የዛፍ ስር የእድርቅ ስርዓት በዚህ ረገድ የሚነሳ አንዱ ተምሳሌት ነው፡፡
ሰው ሁሉ በስብዕናው ብቻ ተከባብሮ እንደሚኖርባት በርካቶች ሲመሰክሩላት የነበረው፣ ብዙዎችም የፍቅር ከተማ ሲሉ የሚያነሷት ድሬዳዋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰላም እሴቷ መሸርሸር መጀመሩ አሳስቦናል ያሉት ተወላጆቿ፣ ለህዝቦቿ የለመዱት ፍቅር ይመለስላቸው ዘንድ ነሃሴ 04 ቀን 2011 ዓ.ም፣ የዛፍ ስር ባህላዊ የእርቅ ፌስቲቫል ተሰናዳ፡፡
የኢትዮጵያዊ አንድነት ተምሳሌት ድሬዳዋ በተዘነጉቱ ባህሏ የእርቅ እሴቷ ተምሳሌታዊ ሰላሟን ታሰፍን ዘንድ፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ እናቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች በዚሁ ፌስትቫል ታዳሚ ይሆናሉ፡፡ ድሬ ዳዋም ከራሷ የተረፈን ሰላምና ፍቅር ለሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ታተርፍ ዘንድ ልጆቿ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
በዚህ የካበተ ባህላዊ የአብሮነትና የፍቅር እሴቷ ዳግም የፍቅር ተምሳሌትነቷንም ለመላው ኢትዮጵያ እንደምታስተምር በተለያዩ ዓለማትና የኢትዮጵያ ክፍል ባሉ ልጆቿ ትልቅ ተስፋ አለ፡፡