በአማራ ክልል ከ4 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ተግባራት ለማሳተፍ እየተሰራ ነው

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ወጣቶችን በያዝነው ክረምት በበጎ ፈቃድ ተግባራት እያሳተፈ ነው፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አባይነህ መላኩ የ2011 ዓ.ም ክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሐምሌ 3፣ 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 129 ወረዳዎች 2 ሚሊየን 425 ሺህ 580 ወጣቶች ወደ ሥራ መሰማራታቸውንም ነው አቶ አባይነህ የተናገሩት፡፡ የተሰማሩባቸው ተግባራትም ማጠናከሪያ ትምህርት፣ ችግኝ ተከላ፣ ጤና እንክብካቤ፣ ደም ልገሳ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች ናቸው ብለዋል፡፡

ቀድመው ወደ ሥራ የገቡትን ጨምሮ በያዝነው ክረምት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ተግባራት ለማሰማራት እንደታሰበም የቢሮው መረጃ ያሳያል፡፡

ከአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ይህም መንግስትና ኅብረተሰቡ ለሥራው የሚያወጡትን 9 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ማስቀረት እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡