የአሸንድዬ፣ ሶለልና ሻደይ በዓላትን አስመልክቶ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሄደ

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ዞን የሚከበረውን የአሸንድዬ ሶለልና ሻደይ በዓላትን አስመልክቶ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ እንግዶችና የክልሉ ተወላጆች ታድመዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ  ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በአለም የሴቶች  ቀን  ማርች 8 የሚታወስ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን፣ የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት የኢትዮጵያ የሴቶች የነፃነት በዓላት ናቸዉ ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም በዓላቱ የአማራና የትግራይ ክልል ህዝቦችን የሚያስተሳስሩ  መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ኢንጅነር እንዳወቅ አብጤ በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል በአደባባይ ያልወጡ ትውፊቶች ያሉት ህዝብ መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉን በቀጣይ ከአዲስ አበባ ባሻገር  እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚከበር ሲሆን፣ ዓላማውም ባህሉን ለትውልድ ማስተላለፍና በዩኔስኮ የሰሜን ኢትዮጵያ የልጃገረዶች በዓል በሚል ለማስመዝገብ ነው ተብሏል፡፡