የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትርን አነጋገሩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ራስሙስ ፕረህንን በዛሬው ዕለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በውይይታቸው ወቅት  ኢትዮጵያና ደንማርክ በሁሉም ዘርፍ መልካም የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ የዴንማርክ መንግስት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በድህነት ቅነሳ፣ ምርታማነትን በማሳደግ እና  የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትሩ ራስሙስ ፕረህን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የለውጥ ሂደት እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙት የሁለትዮሽ ኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍና የፖለቲካ ምክክር መግባቢያ ሰነድ መሰረት ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መንግስት የወሰዳቸውን አርምጃዎች ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠሩ በመሆናቸው ዴኒሽ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት እንዲመጡ እንደሚሰሩም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ 

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ድምጽ በማሰማት እየተጫወተች ያለችው ሚና የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዘርፍ ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ መሰረትኢትዮጵያና ዴንማርክ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ስቶክሆልም በሚገኘው ኤምባሲዋ ዴንማርክን ሸፍና ትሰራለች፡፡