በክልሉ የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብቶችን በተቀናጀ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ በጋራ ለመስራት ውይይት ተደረገ

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት የተቀናጀ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎችን በጋራ ለመስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ።

በዚህ ወቅት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰብለጸጋ አየለ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግስት በክልሉ የሚገኙ የባህል እና የቱሪዝም መስህቦችን ለማጎልበትና ለማሳደግ ከዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት አለው።

በክልሉ የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብቶችን ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ክልሉን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ቢሮ ሃላፊዋ፤ በዚህ ዙሪያም በቀጣይ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር ከዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

ቢሮ ሃላፊዋ የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት የተለያዩ የስራ ክፍሎችም ከኮርፖሬቱ ማኔጅመንት አባላት ጋር በመሆን ጎብኝተዋል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ በበኩላቸው፤ ኮርፖሬቱ ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራ በመመረጡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮርፖሬቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዶክመንታሪዎችና ፕሮግራሞች የክልሉን የባህል ስራዎች በተለያዩ ዶክመንታሪ ፊልሞችና ፕሮግራሞች በማስተዋወቅ በቅንጂት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁንም የክልሉ ባህል እና እሴቶች ላይ ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።