የወሳን ኩነት ምዝገባ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ፣  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ሁለተኛው ሃገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታቲስቲክስ ቀን ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎች እና የሚመለከታቻው አካላት በተገኙበት ተከብሯል፡፡

“የልደት ምስክር ወረቀት ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና አድሏዊ አሰራርን ለማስወገድ መሰረት ነው” በሚል መሪ ቃል ነው የተዘጋጀው፡፡

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የወሳን ኩነት ምዝገባ  ዜጎች ህገ መንግስታዊ መብታቸውንና  ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው ከልደት እና ሞት ጋብቻ እና ፍቺ ምዝገባ የሚገኘው መረጃ ለሃገሪቱ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በዓለም ከ1 ቢሊየን ሰዎች በላይ የማንነት መታወቂያ ሰርተፊኬት እንደሌላቸው በመግለፅ÷ በኢትዮጵያም 65 በመቶዎቹ ህጋዊ መታወቂያ እንደሌላቸው ነው የገለፁት፡፡

ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን የሚመዘገቡ ተማሪዎችም ምዝገባቸው ያለምንም ክፍያ የሆኑ በልደት የምስክር ወረቀት እንዲመዘገቡ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

በ2063 የተያዘው ዘላቂ የልማት ግቡን ለማሳካት በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው የገለፁት፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ዳይሬክተር አደል ሆደር በኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት የተወለዱ ጨቅላ ህፃናትን የማስመዝገብ ባህሉ 3 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን÷ የወሳን ኩነት ምዝገባ ከተጀመረበት በሶስት ዓመታት ውስጥ ቁጥሩ ወደ 20 በመቶ ከፍ ማለቱን አንስተዋል፡፡

በዝግጅቱልጆቻቸውን ለልደት ሰርተፊኬትያስመዘገቡ ወላጆችና አዲስ ጋብቻቸውን በወሳኝ ኩነት ያስመዘገቡ ጥንዶች ከፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡