ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የወጣቱ ሚና የጎላ ሊሆን ይገባል ተባለ

በኢትዮጵያ የአብሮነት እሴት ተጠብቆ እንዲቀጥልና ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት 70 በመቶውን የሚሸፍነው ወጣት ሚና የጎላ ሊሆን ይገባል ተባለ፡፡

ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 1 ሺህ 400 ወጣቶች የተሳተፉበት አገር አቀፍ የወጣቶች የሰላምና የአንድነት ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንንእንዳሉት፤ ወጣቱ በሰላም፣ ሀገር ግንባታ እና ዴሞክራሲ ያለውን ሚና በአግባቡ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

ሰላምን እውን ለማድረግ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥ አይገባም ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ፤ ሁሉም ጥያቄ በሰላም ማዕቀፍ ውስጥ ምላሽ ሊያገኝም እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩላቸው፤ ወጣቱ ሰላምን ለማስጠበቅ በሚደረገው ስራ ግንባር ቀደም መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

የሰላም እጦት ዋነኛ ሰለባ ወጣቱ እንደመሆኑ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም  የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡

 “ወንድማማችነትን በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መድረክ በሰላም ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን  ትብብር በጋራ የተዘጋጀ ነው፡፡

መድረኩ በውይይት የሚያምንና ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርብ ትውልድ መፍጠርን ትኩረት አድርጎ መዘጋጀቱም ተገልጿል።