በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመረጋጋትን ለመፍታት የሴቶችን ከፍተኛ ሚና መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ

በሀገሪቱ የሚፈጠረውን ግጭትና አለመረጋጋት ከመፍታት ረገድ ሴቶች ያላቸውን ሚና በሚመለከት ውይይት ተደረገ፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽንና ሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሲፈጠሩ የመጀመሪያ ተጎጂዎች ሴቶች የመሆናቸውን ያህል ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ሴቶች ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ቅርበት አላቸው ተብሏል፡፡

ሴቶች ልጆቻቸውን፣ ባሎቻቸውና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን በቅርበት የማግኘት ዕድሉ ስላላቸው ችግሮችን መፍታት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን ከመቅረፍ ረገድና ሰላም እንዲሰፍን ሴቶች ጉልህ ሚና እንደነበራቸውም ተጠቁሟል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል ሚናቸውን አልተወጡም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ በሀገሪቱ ሰላን በማስጠበቅ በኩል ሴቶች ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በመጠቀምና ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡