በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የለውጥ ስራዎችን ማስጀመሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የለውጥ ስራዎችን ማስጀመሪያ መድረክ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም በተገኙበት በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሀገራችን የመጀመሪያውን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከሶስት አመታት በላይ ከፈጀ የዝግጅት ምዕራፍ በኋላ ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ፍኖተ ካርታው እስከ 2022 ዓ.ም የሚተገበር ሲሆን፣ 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የትግበራ አመት ይሆናል፡፡ ፍኖተ ካርታው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄዎችን አስቀምጧል፡፡

የስርዐት ትምህርት አዘገጃጀት ይዘትና ትግበራ ችግር፣ የዩኒቨርሲቲዎች በተልእኮ አለመለየት፣ የትምህርት አደረጃጀት ችግር እና ሌሎችም አራት ችግሮች የተለዩ ሲሆን፣ በእነዚህ ችግሮች ምክንያትም የስነምግባርና የሞራል ውድቀት፣ ስርአት አልበኝነትና ምክንያታዊ አለመሆን፣ የስራ ጠባቂነትና ጥገኝነትን የመሳሰሉ ችግሮች በተማሪዎች ዘንድ ተስተውለዋል ተብሏል፡፡

የአንደኛ አመት ተማሪዎችን የታሪክ፣ ጂኦግራፊና አንትሮፖሎጂ፣ የኮምፒውቴሽናል ክህሎት፣ የስነምግባር፣ የቋንቋ፣ የስነ ተግባቦት፣ ምክንያታዊነት፣ ቴክኖሎጂና አለምአቀፋዊ እውቀት ሊያስጨብጡ የሚችሉ ትምህርቶችን መስጠት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ ተልዕኳቸው ትኩረት ማደራጀት ማለትም የምርምር፣ የአፕላይድ ሳይንስ እና ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎች አድርጎ ማደራጀት እና የዩኒቨርሲቲ ቆይታን አራት አመት እንዲሆን ማድረግ ለምህንድስና አምስት ለህክምና ስድስት አመት ለማስተርስ ዲግሪ ሁለት አመት እንዲሁም ለፒኤችዲ ዲግሪ ደግሞ አራት አመት ማድረግ ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ለመፍታት በፍኖተ ካርታው የተቀመጡ የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦች ናቸው ተብሏል፡፡ መረጃው የፕሬስ ኤጄንሲ ነው፡፡