የጦር መሳሪያ በተሽከርካሪ ሲያዘዋውር የተያዘው ተከሳሽ በ2 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

ተከሳሽ አብዱራህማን ዩኑስ ከሚመከለተው የመንግስት ፈቃድ ውጪ ወደ ሀገር እንዳይገቡ ገደብ የተደረገባቸው የጦር መሳሪያዎችን በተሸከርካሪ ደብቆ ወደ ሀገር ሊያስገባ ሲል ተይዞ ዐቃቤ ሕግ በመሰረተው ክስ በእስራት ተቀጥቷል፡፡

ተከሳሽ 53 ቱርክ ስሪት ሽጉጦችንና 35 ሺህ 766 ጥይቶችን የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-A50931 አ.አ በሆነ ላንድክሩዘር መኪና ደብቆ ወደ ሀገር ሊያስገባ ሲሞከር በተደረገው ክትትል በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ክልል ልዩ ቦታው ጣፎ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተሸከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻ ተይዟል፡፡

ተከሳሽ ክሱ በችሎት ተነቦለት እንዲረዳ ከተደረገ በኃላ ድርጊቱን ክዶ በመከራከሩ ዐቃቤ ሕግ እንደ ክሱ አቀራረብ ምስክሮች አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም መዝገቡን መርምሮ ተከሳሽ ሽጉጥና ጥይት በመኪና ደብቆ በፍተሻ ስለመያዙ በመረጋገጡና መከላከልም ባለመቻሉ በተከሰሰበት ድንጋጌ ጥፋተኛ መሆኑን በይኗል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመመልከት ተከሳሽ በ2 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ5 ሺህ ብር መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ምንጭ፡- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ