የአዲሱ የትምህርት መዋቅር 6-2-4 በሚል ማሻሻያ መደረጉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲሱ የትምህርት መዋቅር 6 ዓመት የአንደኛ ደረጃ፣ 2 ዓመት የመለስተኛ ትምህርት እንዲሁም 4 ዓመት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሆን መወሰኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርት ፖሊሲ የውጭ ናፋቂና ሀገር በቀል እውቀቶችን ከመስጠት አንፃር ውንነቶች እንዳሉ በመረዳት የትምህርት ስርዓቱ የሃገሪቱን አንድነት የሚያስቀጥል፣ ከማህበረሰቡና ከተማሪው ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ሃገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አዲሱ የትምህርት መዋቅር በሶስት ክፍሎች ተመድቦ እንደሚሰራ ጠቅሰው፥ 6 ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ 2 ዓመት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም 4 ዓመት ደግሞ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል።

ተማሪዎች 6ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ክልላዊ ፈተናን የሚፈተኑ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት ክልላዊ ፈተና የነበረው 8ኛ ክፍል ደግሞ ሃገራዊ ፈተና ይሆናልም ተብሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት በግል ዘርፍ ተይዞ የቆየው የቅድመ መደበኛ ትምህርት (የህጻናት ማቆያን ጨምሮ እስከ ኬጂ) በግልና በመንግስት እንዲያዝ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡

ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የቆየው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና አይኖርም የተባለ ሲሆን፥ የ12ኛ ክፍል ፈተና ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ሊሆንም ላይሆንም እንደሚችል ተጠቁሟል። በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠናዎች ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።

በዚህም ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ትምህርት መርሃ ግብር ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 8 (እስከ ሶስተኛ ዲግሪ) ደረጃ ድረስ መማር እንደሚችሉም በመግለጫው ወቅት ተነስቷል።

የመምህራን ድልድልን በተመለከተም መምህራኑ ያላቸውን የትምህርት ደረጃ መሰረት ባደረገ መልኩ ይተገበራልም ነው የተባለው።ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መምህራን፣ ለሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) እንዲሁም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው መምህራን የሚመደቡ ይሆናል።

ፍኖተ ካርታው ከ3 እስከ 5 አመታት የሚፈጅ በሆንም መሰረታዊ ተብሎ የተለዩ ጉዳዮች በቀጣይ አንድ ወር በመጨርስ ወደ ትምህርት ማዕቀፉ በእቅድ ደረጃ እንዲገባ ይደረጋል በ2012 አጠቃላይ ስራው አልቆ በ2013 ወደ ትግበራ ይገባል፡፡

ፍኖተ ካርታው ከትምህርት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችንና  ያልተካተቱ ጠቃሚ ጉዳዮች ከማከተቱም በሻገር ትውልዱን ኢትዮጵያዊ  አውቀት እንዲኖረው ያደርጋል ተብሎም ይታሰባል፡፡

ለሀያ አራት ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እንዲሁም እስትራቴጂ ያመጣቸው በጎ ለውጦች ቢበዙም  ዘመኑን  ያላማከለ እንዲሁም  ከፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርትና ስልጠናው ፍኖተ ካርታ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡

ፍኖተ ካርታውን የሚመለከታቸው አካላት ካዘጋጁት በኋላ ከአምስት አመት በፊት ለህዝብ ይፋ ሆኖ  ምክክር ተደረጎበታል፡፡

ከምክክሩና  በኋላም ከ357 በላይ ቢሻሻሉ የተባሉ የመፍትሔ ሀሳቦች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ በዋናነት  36ቱ መሰረታዊ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም ባሻገር በትምህርትና ስልጠናው ፍኖተ ካርታ ከተቀመጡት 37 የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከል ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በተመረጡት 13 የርብርብ መስኮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የትምህርት ሚኒስቴሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ  ገልፀዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ መግለጫቸው ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ መንግስት በመልካም እሴት፣ ስነ ምግባርና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት እንደሚሰራ ተናግረዋል።