የእነ ብርጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞን የክስ መዝገብ ለመመርመር ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእነ ብርጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞ የምርመራን መዝገብ ለመመርመር ለነሐሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ በእነ ጄነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ይግባኝ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለመመርመር በማስፈለጉ ነው ቀጠሮ የሰጠው።

ብርጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞ የብዙዎቻችን ተጠርጣሪዎች የባንክ ደብተሮች በመርማሪ ቡድኑ ስለተያዙብን፣ በቤት ኪራይ የሚኖሩ ቤተሰቦቻችን ለችግር ተዳርገዋል ሲሉ ለችሎቱ አቤት ብለዋል።

የመርማሪ ቡድኑ በበኩሉ ከወንጀሉ ጋር የሚያያዝ ከሆነ የባንክ አካውንት የሚታገድበት እንጂ የባንክ ደብተሩ የሚያዝበት አግባብ እንደሌለ ለችሎቱ አስረድቷል።

የተጠርጣሪዎቹ የባንክ ደብተር እና አልባሳት በቁጥጥር ስር በዋሉባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም መርማሪ ቡድኑ ጠቁሟል።

ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎቹ በምርመራ ሒደት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከሕግ አግባብ ውጭ የተያዙባቸው ንብረቶች እንዲመለሱላቸው ትእዛዝ ሰጥቷል።

እንደ ኢቢሲ ዘገባ የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ በመታሰራቸው ምክንያት የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ችግር ላይ ወድቀዋል በሚል ለችሎት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፣ ለችግር የተጋለጡ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ቀለብ እንዲሰጣቸው ትእዛዝ አስተላልፏል።