የሻዳይ፣አሸንድዬ እና ሶለል ባህል ዓመታዊ ክብረ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት ተከበረ

የሻዳይ፣አሸንድዬ እና ሶለል ባህል ዓመታዊ ክብረ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት ተከበረ፡፡

በዋግ ሹሞች መዲና ሰቆጣና አካባቢዋ ሻደይ፣ በቆቦ አካባቢ ሶለል እና በላስታ እና በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች አሸንድዬ በሚል የሚከበረው የልጅ አገረዶች ጨዋታ በዓል ዛሬ በባህርዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በዚሁ በክልላዊው የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓል አከባበር ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ካሳው እና የተለያዩ የክልል እና የፌዴራል የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከመገፋፋትና ከመጠላላት ወጥተን አንድ ስንሆን የጥበብ አውድማ እና የፍቅር ተምሳሌት እንሆናለን ብለዋል፡፡

ዘመን ባልከለሰው አብሮነታችሁ አምራችሁና ደምቃችሁ ስትታዩ በእርግጥም ‘የአማራ ሕዝብ ታላቅ ነው’ ስንል ያለምክንያት አለመሆኑን ከመግለፁም ባሻገር ጥበብ፣ ኩራት፣ አብሮነትና ጀግንነት የክልሉ ህዝብ መገለጫዎች ማሳያ ጭምር እንደሆኑ ያሳያልም ብለዋል።

የአብሮነታችን አሻራ፣ የአንድነታችን ተምሳሌት እና የፍቅራችን መገለጫ የሆነው የሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰ ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ስራ መጀመሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ “ታላቅ ነን ስንል ራሳችንን አክብረንና አስከብረን ሌሎችንም የምናከብር ህዝቦች ነን ማለታችን ነው፤ ታላቅ ነን ስንል ችግር በገጠመን ጊዜ አንድ ሆነንና ተባብረን ከችግር የምንወጣ ብርቱ ህዝቦች ነን ማለታችን ነው፤ ታላቅ ነን ስንል በችግር አረንቋ ውስጥ ያሉ ሌሎች ህዝቦችን የምንታደግ ህዝቦች ነን ማለታችን ነው›› በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሻዳይ፣አሸንድዬ እና ሶለል ባህል በዩኔስኮ በማይዳሰ ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ስራ መጀመሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛት አብዩ በበኩላቸው የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓል ራሱን የቻለ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ሁነቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ ግዛት፤ የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ባህላዊ ክዋኔዎቹ ሳይበረዙ እና ሳይከለሱ የባህሉ ባለቤት በሆነው ሕዝብ ተጠብቀው፣ ተናፍቀው እና ተወዳጅነታቸውን አጎልብተው እንዲዘልቁም ይደረጋል ብለዋል።