በ67 ሚልዮን ብር ወጪ የተገነባው ሰንዳፋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

​​​​በ67 ሚልዮን ብር ወጪ የተገነባው ሰንዳፋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለዋልታ እንዳሉት፤ ክልሉ ለጤናው ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሉ ከአምስት ወራት በፊት ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ እስካሁን ከ5ሺህ በላይ ታካሚዎች መገልገላቸውን ነግረዉናል።

በሆስፒታሉ ውስጥ ህክምናውን ሲከታተል ያገኘናቸው ታካሚ  እንደሚገልጹት፤ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ጥሩ መሆኑን የተሻለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሆስፒታሉ በአቅራቢያው በመገንባቱ ቀድሞ አዲስ አበባ እየሄደ ሲታከም ያወጡት የነበረውን ወጪም እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የመድሃኒት እጥረት መኖረን የጠቆሙት ታካሚው፤ በቀጣይም እጥረቱ ተቃሎ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት የታማሚዎችን ጤና እንደሚመልስ ተስፋ ማድረጋቸውን ነግረውናል።

በሰንዳፋ በኬ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሆስፒታሉ 100 የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት እና ለ450ሺህ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል 85 ሆስፒታሎች እና 1450 ጤና ጣቢያዎች መኖሩን ያመለከቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ደረጄ፤ በቀጣይ በተለይ በጥራት ላይ አተኩረው  እንደሚሰሩ ተናግረዋል።