አቶ በቀለ ሙለታ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ

አቶ በቀለ ሙለታ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ለአምስት ዓመታት የመሩት አቶ በቀለ ሙለታ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር የቀድሞው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዱ ይመሰል ከዚህ በፊት የጀመሩትን የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመቀጠል የስራ አመራር ቦርዱን ጠይቀው በተፈቀደላቸው መሰረት ነው አዲስ ኃላፊ የተሾመው።

በአክሲዮን ማህበሩ ስራቸውን የጀመሩት አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በቀለ ቀደም ብሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በጋዜጠኝነትና በአመራር የካበተ ልምድ አላቸው።

አቶ በቀለ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ዘርፍ የያዙ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ተቋሙ ከተጠሪነት ወጥቶ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን የመሪነት ሚናቸውን ተጫውተዋል።

በዚህም ኢዜአ ከቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተጠሪነት ተላቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ለመሆን ችሏል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አክሲዮን ማህበር የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመሰል በተቋሙ ከጋዜጠኝነት እስከ ዋና ስራ አስፈፃሚነት ከምስረታው ጀምሮ ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።