ቄራ ጎፋ ማዞሪያ አካባቢ በሁለት የፖሊስ አባላት የተፈፀመውን ድርጊት እያጣራሁ ነው -የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮሚሽን

ነሃሴ 20 ቀን 2011 ዓ/ም ከረፋዱ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ቄራ ጎፋ ማዙሪያ አካባቢ በድለላ ስራ ላይ በተሰማሩ ሁለት ቡድኖች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡

የተፈጠረውን አለመግባበት ለመዳኘት ወደ ቦታው ያቀኑ ሁለት የፖሊስ አባለት ያለመግባባቱን ለማብረድ የሁለቱም ቡድን አባለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄዱ በሚጠይቁበት ወቅት አለመግባባቱ ተካሮ የፖሊስ አባላቱ ጥይት መተኮሳቸውና በሰዎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
 

የፖሊስ አባለቱ አዲስ እና በቅርቡ ሰራዊቱን የተቀላቀሉ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውሶ ነግር ግን የፈፀሙት ድርጊት ተገቢነትና ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ ጉዳያቸው በወንጀልና በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 
 

ጉዳዩን አጣርቶ የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑ የገለፀው ኮሚሽኑ ፤ ህብረተሰቡ መሰል ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በየደረጃው ለሚገኙ የስራ ኃላፊዎች የማሳወቅ ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

(ምንጭ ፦የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮሚሽን)