ባለፉት ሶስት ዓመታት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻል ማሳየቱ ተገለጸ

በጤና ሚኒስቴር ፣ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና አጋር ድርጅቶች ሲካሄድ የቆየ ጥናት ዛሬ ይፋ በሆነበት መድረክ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻል ማሳየቱ ተገልጿል።

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅና የተሻለ የጤና አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመቀየስ በሚል ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት  ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ጥናቱ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በአገር-አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 305 የቆጠራ ጣቢያዎች መካሄዱ ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት እድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ማለትም በመዉለድ የዕድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ 8 ሺህ 885 ሴቶች  የጥናቱን መረጃ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ 

ለክትባት መረጃም ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 3 ዓመት የሆናቸው 1 ሺህ 28 ህጻናት እንዲሁም ለቁመትና ክብደት ልኬት ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 4 ሺህ 990 ልጆች በጥናቱ ተካተዋል፡፡

በዚህም የቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም በ2008 ዓ.ም ከነበረበት 31 በመቶ  ወደ 41 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ የተቻለ ሲሆን በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥርም 50 በመቶ መሻሻል እንዳሳየ ተመልክቷል፡፡

በቀጣይ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የጤና  ሚኒስቴር  አዳዲስ የጤና አገልግሎት ሥርዓቶችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ገልፀዋል።

ከ5 ዓመት በታች የሕፃናት ሞት አሁን ላይ ከ1ሺህ ሕፃናት ውስጥ 55 ህፃናቶች እንደሚሞቱ  ጥናቱ ያመለከተ ሲሆን፤ ይህም በ2008 ዓ.ምት ከነበረው 65 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ለውጥ መምጣቱንአሳይቷል ተብሏል፡፡ 

ዋና ዋና የጥናቱ ጠቋሚ መረጃዎች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደበት  ሲሆን፤ ከውይይቱ የተገኙ ነጥቦችም በቀጣይ በዘርፉ ለሚሰሩ ስራዎች በግብዓትነት ያገለግላሉ ነው የተባለው።

ጥናቱ እውን እንዲሆን የዓለም ባንክ ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ዩኒሴፍ የቴክኒክና የበጀት ድጋፍ አድርገዋል፡፡