በምዕራብ ሸዋ ዞን የአዋሽ ወንዝ ያስከተለው ጎርፍ የተዘራ ሰብል ላይ ጉዳት አደረሰ

በምዕራብ ሸዋ ዞን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰስ ያስከተለው ጎርፍ 3ሺህ 500 ሄክታር የእርሻ ማሳ ላይ የተዘራ ሰብልን ከጥቅም ውጪ ማድረጉን የዞኑ ኮሙዩኔኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጉታ ቡልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጎርፉ ያደረሰው ጉዳት ኤጀርሳለፎ እና ኤጄሬ በተባሉ ወረዳዎች በሚገኙ 12 ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

በዚህም በ3ሺህ 500 ሄክታር ማሳ በመጥለቀለቁ ተዘርቶ የነበረ የስንዴ፣ የበቆሎ፣የማሽላና ሌላም ሰብል ከጥቅም ውጭ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከጥቅም ውጪ የሆነው ሰብል ከ12 ሺህ በላይ አባወራ አርሶ አደሮች የዘሩት እንደነበር ጠቁመው፤ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በመቀጠሉ በጎርፍ የሚጥለቀለቅ ማሳ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ለተጎጂዎቹ  መፍትሄ  ለመስጠት ጥናት የሚያካሂድ ቡድን መቋቋሙንና ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን ጎርፍ ለመከላከል የአካባቢው ህብረተሰብ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደረግም ማሳሰባቸው ተጠቁሟል።