በህገ-ወጥ መንገድ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የገቡ 30 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ አገኙ

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መንግሥት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሩ ለገቡ 30 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ሰጠ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጋር ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሁለትዮሽ የሥራ ሥምሪት ሥምምነት ተፈራርሟል።

በሥምምነቱም መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት ከቤት ሠራተኝነት በተጨማሪ በሌሎች ሙያዎች ግለሰቦችን በማብቃት ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ለመላክ ውጥን አለው።

ይህንንም ተከትሎ ከሥምምነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬተስ የመጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ግለሰቦቹ የሚሰለጥኑበትን ሥፍራዎች ለመጎብኘት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ሃላፊዎቹ የህክምና ኮሌጆች፣ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም ሌሎች የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ይጎበኛሉ ተብሏል።

ይህንን በተመለከተ በተዘጋጀው መርኃ ግብር ላይ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ኤርጌጎ ተስፋዬ ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከሥምምነቱ አስቀድሞ ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በሕገ-ወጥ መንገድ የገቡ 30 ሺህ ዜጎች ህጋዊ የሥራ ፍቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ለዚህም የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መንግሥት አመስግነው ከዚህ በኋላ እንዲህ ያለው ምህረት እንዳማይደረግ አስረግጠው ተናግረዋል።

የተባበሩት አረበ ኢሚሬትስ ከዚህ ቀደም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚታይባትን ክፍተት ጥብቅ ማድረጓን ገልጸው ኢትዮጵያም ተመሳሳይ አቋም አላት ነው ያሉት።

ለአብነትም በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በሕገ-ወጥ መልኩ ይንቀሳቀሱ ከነበሩ 130 ኤጀንሲዎች መካከል 94ቱ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸው 36 ብቻ እንዲሰሩ ተደርጓል።

በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት 549 ኤጀንሲዎች መኖራቸውን ገልጸው በሦስት ማኅበራት እንዲታቀፉ በማድረግ የቁጥጥር ሥርዓቱ ጥብቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስን ጨምሮ ከአራት የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር የሥራ ሥምሪት ሥመመነት ተፈራርማለች።

(ምንጭ፦ኢዜአ)