በ2011 ዓ.ም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢተሰበሰበ

በ2011 ዓ.ም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢተሰበሰበ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ለግድቡ ግንባታ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከህዝብ በተደረገ ድጋፍ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።

በ2011 በጀት ዓመት ሁለት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን እና የውጭ ዜጎች ግድቡን መጎብኘታቸውንና የተለያዩ ተቋማትም የጉብኝት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑንም ጽቤቱ በላከው መግለጫ ጠቅሷል።

ፅህፈት ቤቱ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ መረጃዎችን በስፋት ለህብረተሰቡ በማድረስና በቦንድ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እየሰራሁ መሆኑን አስታውቆ፤ ከሚመለከታቸው የገንዘብ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በቦንድ አሻሻጥና አመላለስ ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ላይ መሆኑን ገልጿል።

በቀጣይ በጀት ዓመትም ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን ጠቁሟል፡፡

ነዋሪዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ ተቋማት በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በሞራል ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን በአዲሱ ዓመት የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲልም ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡