ባለሀብቶቹ 12 የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ ግንባታ ሊቀይሩ ነው

በአማራ ክልል የሚገኙ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የክልሉ መንግስት ከባለሀብቶች ጋር መክሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ ልማት ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር ነው የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የተወያዩት።

በክልሉ ልማት ላይ የተወያዩት ባለሀብቶችም 12 የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ ግንባታ ለመቀየር ወስነዋል።

በውይይታቸውም "አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የተማሪዎች መማሪያ ትምህርት ቤቶች አሉን፤ አብዛኞቹንም ለመቀየር የክልሉ መንግስት፣ አጋር አካላት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብርቱ ጥረት አድርገዋል፤ ቀሪዎቹን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የቻላችሁትን እንድታደርጉ ጥሪ ቀርቦላችኋል" ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡ 

በ2012 ዓ.ም አንድም የዳስ ትምህርት ቤት እንዳይኖር እየሰራን ነው ያሉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ባለሀብቶቹ የቻሉትን ያክል አሻራቸውን በማሳረፍ ትውልድ የመቅረፁን ሥራ ለማገዝ ፈቃደኞች ስለሆኑ አመስግነዋቸዋል፡፡

ከሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት፣ ጃናሞራ እና ጠለምት ወረዳዎች ላይ ስድስት ትምህርት ቤቶች፤ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ጋዝጊብላ፣ አበርገሌ እና ሰሃላ ሰየምት ወረዳዎች ላይ ስድስት ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 12 ትምህርት ቤቶችን ከዳስ ወደ "ክላስ" ለመቀየር ባለሀብቶቹ ቃል ገብተዋል፡፡

ሁለት ባለሀብቶች በጋራ አንድ ትምህርት ቤት ለመስራት ቃል ሲገቡ፣ ዘጠኝ ባለሀብቶች አንድ፣ አንድ ትምህርት ቤት እና አቶ ወርቁ አይተነው የተባሉ ባለሀብት ደግሞ በሁለቱም ዞኖች በሁለት ወረዳዎች ውስጥ ሁለት ትምህርት ቤት ለመገንባት ቃል መግባታቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡