ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል 9ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደረጃ በታች እንደሚገኙ እና አብዛኞቹ እንደ አዲስ የሚሰሩ በመሆናቸው የማሻሻል ስራ እያከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም  በክልሉ  የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ በተሰራው  ስራ በርካታ ለውጦች  ቢታዩም ጎን ለጎን  የዳስና የዛፍ ስር ትምህርት ቤቶች እንዲለወጡ  አለመደረጉን እንደ ድክመት አንስተዋል።

በተለይ በየዞኑ ያሉትን የትምህርት ቤት ደረጃዎች ያሉበት ሁኔታ አለማሳወቅና የውሸት ሪፖርቶች መበራከት ችግሩ እንዲሰፋ ማድረጉንና ለቀጣይ ይህ እንዳይከሰት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

መንግስት ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻልና የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ለማድረግ እየሰራ ቢሆንም፤ ሁሉንም ለመገንባት አቅም ይጠይቃል ያሉት ሀላፊው ከባለሀብቶችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡