ኤቢኤች የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲን ከሰሰ

ኤቢኤች የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲን ከሰሰ

ኤቢኤች (ጥምረት ለተሻለ ጤና) ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት የድርጅቴን ስምና ዝና በማጥፋት ተግባር እና በድርጅቴ ላይ ኪሳራ አድርሶብኛል ያለውን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከሰሰ።

አማካሪ ድርጅቱ ስምና ዝናዬን በማጥፋት ተግባር 174 ሚሊየን 636 ሺህ 893 ብር ከ40 ሳንቲም ብር ጉዳት ካሳ እንዲከፈልና ሌሎች የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰድ ለማስወሰን በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ላይ ክስ መመስረቱን አሰታውቋል፡፡  

ከሳሽ የንግድ ተቋም እንደሆነና ከአገርው ስጥና የውጭ ደርጅቶች ጋር ውል በመግባት አገለግሎት ያቀርባል፡፡ በዚህ መሰረት የጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ በከፈተው የአገልግሎት ማዕከል ላለፉት ስድስት ዓመታት የቤተሙከራ፣ ቤተመጽሐፍትና ሌሎች አገልግሎቶችን ሲያቀርብ መቆየቱ ገልጿል፡፡  

ውሉ እስከ ታህሳስ 21/2010 ዓ.ም የሚቆይ እንደነበርና ከፍተኛ የመንግሰት የሥራ ኃላፊዎችና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ የሚያውቁት እንደነበር ታውቋል፡፡

ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ ‹‹ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም›› በማለት እግድ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።

በዚህ መሰረት የከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ የፍተሐብሔር ችሎት ለጳጉሜ 5፣ 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ኤጀንሲው ለመስከረም 26፣ 2012 ክሱ ደርሶት መልስ እንዲያመጣ ተጠይቋል፡፡ ክሱን ለመስማት ደግሞ ጥቅምት 24/2012 ቀን ተቆርጧል፡፡