የሚዲያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በአዎንታዊ መንገድ መሆን እንዳለበት ተገለፀ

የአፍሪካ ወጣቶች ባህላቸውንና ታሪካቸውን ሳይለቁ የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ መሳሪያዎችን ለአዳዲስ ነገሮች ፈጠራና ለአዎንታዊ ተግባራት ማዋል እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች፡፡

ብጹእ ካርድናል ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ትናንት በአፍሪካ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ማህበር “ሲግኒስ አፍሪካ ኮንግረንስ” የተሰኘና ትኩረቱን በአፍሪካ ወጣቶች የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ መሳሪያዎች አጠቃቀም ዙሪያ ኮንፈረንስ ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ ከአፍሪካ 60 በመቶ የሚሆነው ወጣት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ መልክ ሊይዝ ለሀገርና ለወገን አዎንታዊ ፋይዳ በሚያበረክት መልኩ ሊቃኝ ይገባዋል፡፡

ጊዜው በአፍሪካ ዘመናዊ የኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች የጎሉበት ነው ያሉት ካርዲናሉ ፤ወጣቱ ሚዲያውን ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለጋራ እድገት፣ የሰዎችን ክብር በማይነካ ሥልት፣ ባህልና ታሪካቸውን በሚያጠናክር ሁኔታ መጠቀም ይገባዋል ሲሉ መክረዋል፡፡

ወጣቶች በር ዘግተው አንድ ኮምፒዩተርና ስልካቸው ላይ ረጅም ጊዜያቸውን ከማጥፋት መቆጠብ አለባቸው፡፡ ዓለም ሰፊ እንደሆነች፣ በአካባቢያቸው ያለውን የራሳቸውን ሕብረተሰብ መመልከት ፣በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ጠቅሰው፣ በግል ጉዳያቸው ላይ ብቻ እንዳያተኩሩ ካርድናል ብርሃነ ኢየሱስ አደራ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑት አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው ፤ ይህ የአፍሪካ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ማህበር ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ካስቻሉት ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከፍተኛ በመሆኑና በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለስብሰባዎች ተመራጭ እያደረጓት መምጣታቸውን ገልጸው፣ የሚዲያ ቴክኖሎጂም ከዚህ ተነጥሎ የሚታይ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት