በገቢዎች ሚኒስቴር የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፓርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ  የህፃናት ማቆያ አስመረቀ

በገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ቦሌ ኤርፓርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ  የህፃናት ማቆያ የህፃናት ማቆያ ማዕከል አስመርቋል።

የህፃናት ማቆያ ማዕከሉ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል፡፡

የገቢዎች ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ምህረት ምንያስብ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ እናቶች ልጆቻቸውን የሚንከባከቡበትና በስራቸው ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር ግድ ይላል፡፡

በመሆኑም ሀገር ወደተሻለ ደረጃ እንድትሸጋጋር የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወሳኝ በመሆኑ በተለይ በየመስሪያ ቤቱ ለሚወልዱ እናቶች ልጆቻቸውን የሚንከባከቡበት አመቺ ስፍራን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ነው የገለፁት፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው  በመስሪያ ቤቱ የሚገኙ ሴቶች ተቋሙን ወደተሻለ ደረጃ የማሳደግ አቅም እንዳላቸው ጠቁመው፤  የዚህ ህፃናት ማቆያ መከፈትም የሰራተኞቹን ጫና የሚቀንስና ተቋሙንም ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም መሰል  የህፃናት ማቆያ ማዕከል በሌሎች ቅርንጫፎች እንደሚተገበርም ነው የተናገሩት።

በሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የህፃናት ማቆያ እንዲከፈት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነና ይህም  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተነግሯል።

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች የህፃናት ማቆያ ማዕከል ባለፈው ሀምሌ ወር ለምረቃ መብቃቱ ይታወሳል፡፡