የብሄራዊ ኩራት ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ ተከበረ

የብሄራዊ ኩራት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ “አዲስ አበባ ቤቴ ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ” በሚል መሪ ቃል በሚሊኒየም አዳራሽ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል፡፡

የፌደሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በዚሁ ወቅት አንዱ ብሄር ለሌላው ብሄር ክብር እና የኩራት ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንዱ ሀይማኖት ለሌላው ሀይማኖት ኩራትና ክብሩ ነው ያሉት አፈጉባኤዋ፤  ሁሌም እንደኮራንና እንደተከባበርን እንድንቀጥል ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ህብረ-ብሄራዊነቱንና አንድነቱን  እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አፈ ጉባኤዋ አክለውም ኢትዮጵያ የምትባል የገናና ታሪክ ባለቤት፣ የስልጣኔ መሰረትና ተምሳሌት የሆነች የሀገር ያለችን ኩሩ ህዝብ ነን፣ ኢትዮጵያውያን ተከባበረንና ተደጋግፈን ማደግ እንደምንችል በተግባር ለዓለም ህዝብ አሳይተናል ብለዋል።

ቀጣዩ የ2012 አዲስ ዓመትም የሁሉም የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ ዓመቱ የደስታና የኩራት ጊዜ እንዲሆን ተመኝተዋል።

በርካታ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎችም  በዚህ በዓል ላይ ታዳሚ ሆነዋል፡፡