ፍትህ የነገሰባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ

የፍትህ ቀን  “ፍትህን ማረጋገጥ ይደር የማንለው ስራችን ነው!”በሚል መሪ ቃል በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡ 

በተለይም የፍትህ ቀን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተከበረበት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአንድ ሀገር የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል የሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ መላውን ህብረተሰብ ማካተት እንደሚገባው ገልፀው ፤ የቱን ያህል ምርጥ ስትራቴጂ ቢኖር የትም መድረስ አይቻልም ብለዋል፡፡

ፍትህ የሚጀምረው ከግለሰብ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ግዴታውን በአግባቡ ተወጥቶ መብቱን የሚጠይቅ ዜጋ ባልተፈጠረበት ሃገር ፍትህ ብሶት የምታስተናግድ እንጂ እንባ የምታብስ ልትሆን አትችልም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የሀገሪቱን የፍትህ ስርዓት ለማስተካከልና በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም የሚደረጉ ጥረቶች አሳታፊ በሆነ መንገድ ሊተገበሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

“ፍትህ የጠፋ ዕለት እኔም ሆነ ሀገሬ የለንም” ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ፍትህ የነገሰባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡