የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስራው እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የ2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ልዩ ትኩረት በመሥጠትና ሙሉ የሰው ሃይሉን በማሰማራት ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንዳሉት በበዓላት ወቅት የሰው እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ከወትሮው በተለየ መልኩ ስለሚጨምር ይህንን ታሳቢ በማድረግ በገበያና በመዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም በከተማችን በተለያዩ አካባቢዎች የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰትና ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡

ህብረተሰቡ የፀጥታ ጉዳይ የጋራ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝና ከዚህ ቀደም የተከበሩ ሃይማኖታዊ እና ብሄራዊ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ኮሚሽኑ አስታውሶ አሁንም እንደተለመደው ራሱን ከወንጀል እና ከትራፊክ አደጋ በመጠበቅ ለፀጥታ ሃይሉ የሚያደርገውን ትብብርና የሚሰጠውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት በነፃ የስልክ መስመር 991 እና 816 ወይም በ011-1-11-01-11 መጠቀም እንደሚችል ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡