በአዲሱ ዘመን በኢትዮጵያ የታላቅነት የጉዞ ብስራት የሚታወጅበት ይሆናል- ም/ጠ/ ሚ ደመቀ መኮንን

የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዲሱ ዘመን በኢትዮጵያ የታላቅነት ጉዞ ብስራት የሚታወጅበት እና የብልፅግና መሰረት በጋራ የሚጣልበት እንደሚሆን በአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2012 ዓ. የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልክታቸው በአዲሱ ዘመን በሃገራችን የታላቅነት ጉዞ ብስራት የሚታወጅበት እና የብልጽግና መሰረት በጋራ የምንጥልበት ይሆናልም ብለዋል።

በአሮጌው ዓመት ከድህነት የሚመነጩ እና ወደ ፊት የማያራምዱ እኩይ አስተሳሰቦችን አራግፈን መሻገር ይኖርብናል በማለት የብሩህ ተስፋ መልዕክት የሰነቀ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ማቅ አውልቀን ግምጃ እንልበስ!” በሚል ቅን እሳቤ ለኢትዮጵያ ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ዘመን ለሁላችንም የሰላም፥ የስራ፥ የአንድነት፥ የትብብርና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጽህፈት ቤትም አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ዘመኑ የሰላም የደስታና የብልጽግና እንዲሆንም ተመኝቷል።

በ2011 ዓ.ም በኢኮኖሚ፣ፖለቲካ፣ ማህበራዊና የውጭ ግንኙነት መስኮች ጉልህና ወሳኝ ስኬቶች የተመዘገቡበትና አገራዊ ፈተናዎች የተመዘገቡበት መሆኑም ፅህፈት ቤቱ አስታውሷል።

ያለፈውን ዓመት መለስ ብሎ በመቃኘት ለመጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ብልጽግና ከመላው ኢትዮጵያውን ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ፅህፈት ቤቱ አረጋግጧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የ2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫን አስመልክቶ በአገር ውስጥም በውጭም ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን ዘመኑ የሰላምና የስኬት እንዲሆን ተመኝቷል።

የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የመንግስት ድርጅቶችና ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ማስየተላለፋቸውን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።