ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በዛሬው ዕለት ከካፋ ዞን ነዋሪዎች ጋር በቦንጋ ከተማ ተወያይተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር ለስራ ጉብኝት ካፋ ዞን፣ ቦንጋ ከተማ ሲገቡ በከተማዋ  ስታዲየም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

መንግስት ዜጎች ተከባብረው የሚኖሩባት ታላቋን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያደርገውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በውይይቱ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

የካፋ ህዝብ እንደ ህዝብ ከሰው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የኖረ አስተዋይ ህዝብ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ከቂም፣ ተንኮልና ባለፈ ታሪክ መነታረክ ከድህነት ውጪ የሚያሥገኘው ጥቅም አይኖርም ብለዋል፡፡

በትብብርና በመደመር በመሥራት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ጊዜው አሁን መሆኑን በንግግራቸው አፅንዎት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐብይ መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የክልል አደረጃጀት ለውጥ የሁሉም ጥያቄ መልስ አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ተያያዥነት ያላቸው አማራጭ አሰራሮች መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በውይይቱ ነዋሪዎቹ በክልል ከመሰረተ ልማት፣ ከጤና ተቋም ግንባታ እንዲሁም ከመደራጀት መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ ዞኑ ባለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን ኢንቨስትመንት እንዲመቻች ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳም እና የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በውይይቱ ተሳትፈዋል።