የኢጋድ አባል አገራት የሚጠቀሙበት የካንሰር ህክምና ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

በ450 ሚሊየን ዶላር ወጪ የኢጋድ አባል አገራት የሚጠቀሙበት የካንሰር ህክምና ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት /ኢጋድ/ የተወሰነዉ የካንሰር ህክምና ማእከል በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለሚኖሩ 260 ሚሊዮን ሰዎችን ማእከሉ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ታዉቋል፡፡

ማእከሉ በአዉሮፓዉያኑ ዘመን አቆጣጠር 2020 ጥር ወር ላይ የመሰረት ድንጋይ እንደሚጣልና ግንባታዉም በ450 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

ለማእከሉ ግንባታ በከተማ አስተዳደሩ መሬት የተዘጋጀ እንደሆነና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር አሚር በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል እየተደረገ ባለዉ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ተገኝተዉ ማእከል ግንባታ እዉን ከማድረግ አኳያ ለቀጣናዉ አባል ሃገራት ከፍተኛ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ግንባታው በሁለት አመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቀጠናዉ አባል ሃገራት መሪዎችና ኢጋድ እንዲሁም የአዉስትራሊያ፣ የጀርመን እና ሌሎች ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ለማእከሉ ግንባታ የሚያስፈልገዉ ወጪ በማሰባሰብ ጊዜ እንዳይፈጅና ግንባታዉ ተጠናቆ ቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ ለማስቻል የኢትዮጵያ መንግስትም የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ የተገኙት የሳዉዲ አረቢያ አምባሳደር በኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚ አብዱላሂ በበኩላቸዉ፣ ለማእከል ግንባታው አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ በመንግስታቸዉ በኩል በሙሉ ፍቃደኝነት ድጋፋቸዉን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

የካንሰር በሽታ በአሁኑ ወቅት በአለምአቀፍ ደረጃ በገዳይነቱ ቁጥር አንድ ከሚባሉ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ግንባር ቀደም መሆኑ ይገለፃል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የካንሰር በሽታ በሁሉም የእድሜ ክልል እና ፆታ በሽታዉ ቁጥሩ ከፍ እያለ እንደመጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡