በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት የተገነቡ ስድስት ት/ቤቶች በ2012 ዓ.ም ስራ ይጀምራሉ

በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ከሚገነቡት ትምህርት ቤቶች ስድስቱ  ለ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፈንታ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከትምህርት ቤቶቹ መካከል አራቱ ለማስተማር ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ከአራቱ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ ቁስቋም ትምህርት ቤት በሚል የተሠራው ፕሮጀክት ግንባታው መጠናቀቁን እና ትምህርት ቤቱ ተቀይሮ ለሕጻናት ማሳደጊያ እንዲሆን መወሰኑን አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡  ሰበታ ላይ የሚታደሰው የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤትም ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል ፡፡

ለማስተማር ዝግጁ ከሆኑት መካከል በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ አስተዳድር ላይ የሚገኘው የሎዛ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚገኝበት አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡ 

ከሎዛ ማርያም ትምህርት ቤት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት የሊበን ጭቋላ፣ የጉጂ እና የጃኮ ትምህርት ቤቶችም ለማስተማር ዝግጁ የተደረጉ ናቸው፡፡ 

የሎዛ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመንገድ ችግር ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ሥራው ባይጠናቀቅም ለሥራ ዝግጁ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ክፍሎች እንደተዘጋጁ እና ቀሪ ሥራዎች ከትምህርቱ ጎን ለጎን እንደሚሠሩም ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት ከሚገነቡት አዳዲስ 19 ትምህርት ቤቶች እና አንድ የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት እድሳት ውስጥ ስድስቱ ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ በ2012 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቅቆ በ2013 የትምህርት ዘመን ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡