አስተዳደሩ የ100 የኩላሊት ህሙማንን የአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት ወጪ ሸፈነ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በገንዘብ እጦት ምክንያት የኩላሊት እጥበት ማድረግ ላልቻሉ 100 ህመምተኞች ለአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት ማድረግ የሚያስችላቸውን የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ህመምተኞቹ በሃኪም የታዘዘላቸውን የኩላሊት እጥበት መርሃ ግብር ሳይቆራረጥ በሳምንት ሶስት ቀን ለአንድ ዓመት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

የኩላሊት ህመምተኞቹ ላለፉት በርካታ ጊዜያት በሳምንት የታዘዘላቸውን የሶስት ቀን የኩላሊት እጥበት መርሃ ግብር በገንዘብ እጥረት ምክንያት ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ኢ/ር ታከለ ኡማ እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ህክምና ክፍሎች በመዘዋወር ታካሚዎችን አነጋግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የኩላሊት እጥበት ለሚያከናውኑ ህመምተኞች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያፈላልግ ኢ/ር ታከለ ኡማ በጉብኝታቸው ወቅት ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ በጳውሎስ ፣ ዘውዲቱ እና ሚኒሊክ ሆስፒታል ተኝተው ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ 100 የኩላሊት ህመምተኞች የተደረገ ሲሆን፤ በገንዘብ ሲተመን ከ9 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን  ከከንቲባ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።