የከተማ አስተዳደሩ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነባር አብያተ ክርስቲያን የይዞታ ማረጋገጫ አዘጋጅቶ ለቤተክርስቲያኗ አስረከበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለረዥም ጊዜያት ጥያቄ ስታቀርብባቸው ለነበሩ 15 ነባር የቤተ ክርስቲያኗ ይዞታዎች የተዘጋጁ ካርታዎችን በዛሬው ዕለት ቅዱስ ፓትሪያርኩ በተገኙበት አስረክበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለቤተክርስቲያኗ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄዎች በቀጣይነት ምላሽ እንደሚሰጥ ኢ/ር ታከለ ኡማ በርክክቡ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ለቤተ ክርስቲያኗ የዘመናት የይዞታ ጥያቄዎች በጎ ምላሽ በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በቀጣይም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተመካከረች እንደምትሰራ እና አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎችን ለመደገፍ የሚሰራውን ስራ በዘላቂነት እንደምትደግፍ ቅዱስ ፓትሪያርኩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ኢ/ር ታከለ ኡማ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመናት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ላበረከቱት ጉልህ አስተዋፅኦ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

(ምንጭ፡- የከንቲባ ጽ/ቤት)