የደመራ በዓል ተከበረ

የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማንያን ዘንድ ተከበረ፡፡

ይህ በዓል የሚከበረው በ326 ዓመተ ምህረት መስከረም 17 የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ፍለጋ የጀመረችበት ዕለት መሆኑ ይነገራል፡፡

በተለይ የደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በመከበር ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳን ጨምሮ ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ቱሪስቶች እንዲሁም በርካታ የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችም በተገኙበት ተከብሯል፡፡

በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት የሆነውን ሰላም እና አንድነት መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመዘላለፍ በመተባበር ከመጠላላፍ በመደጋገፍ ላይ ትኩረት በማድረግ የሀገር አንድነትን ፣ ሰላምን እና ፍቅርን እንዲያስቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓሉን የሚመለከቱ ወረብ እና ዝማሬዎች በጽርኃ አርአያም ቅዱስ ሩፋኤል ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቀረበ ሲሆን፤ በዓሉን የሚወክሉ ትዕይንቶችም ቀርበዋል፡፡ የማህበረ ቅዱሳን አባላት እና መስማት የተሳናቸው የሰንበት ት/ቤት አባላትም እየዘመሩ በታዳሚያኑ ፊት አልፈዋል፡፡

ለበዓሉ የተዘጋጀው ደመራ ከከተለኮሰ በኋላም የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ የደመራ በዓል በክልል ከተሞችም ተከብሯል፡፡

በዓሉ በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልድያና፣ ደብረ ማርቆስ በትግራይ ክልል መቐለ፣ አዲግራትና፣ ዓጋመ በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ አሰላና በሌሎችም ከተሞች ተከብሯል፡፡   

በተጨማሪም በቤኒሻንጉል ክልል አሶሳ ከተማን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች በዓሉ ተከብሯል፡፡

የደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት /ዩኒስኮ/ በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡