የደመራ በዓል በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

በርካታ የኃይማኖቱ ተከታዮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ተቀማጭነታቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉ የውጪ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች በስፋት የታደሙበት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተከረው የደመራ በዓል በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በተያዘው ዓመት በርካታ ህዝብ የታደመባቸው ሃይማኖታዊ እና ስፖርታዊ ዝግጅቶች በሰላም መከበራቸውን ኮሚሽኑ አስታወሶ፣ የዘንድሮ የደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ በዋናነት ደግሞ የአዲስ አበባ ወጣቶች እያበረከቱት ላለው ቀና ትብብር እንዲሁም በፀጥታው ስራ ላይ ሃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ መላው የፀጥታ አካላት ኮሚሽኑ ላቅ ያለ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ዛሬ መስከረም 17 ቀን 2012 ዓ.ም የሚከበረው የመስቀል በዓልም በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በድጋሚ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በኢትዮጵያ በርከታ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት ከሚያከብራቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓል ተጠቃሽ ነው፡፡
(ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን )