የጀርመን ተራድኦ ድርጅት በሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ የሚያስችሉ የመቆጣጠሪያ መሳሪዎች ለገሰ

የጀርመን ተራድኦ ድርጅት በሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ የሚያስችሉ የመቆጣጠሪያ መሳሪዎች ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አበረከተ፡፡

መሳሪዎች ዘጠኝ የተለያዩ አይነት ያላቸው ሲሆን፣ በሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ መቆጣጠር የሚያስችሉ በመሆናቸው የኢንዱስትሪ ስፋት ላላቸዉ ለ5 ክልሎችና ለፌዴራል መስሪያ ቤት ተሰጥተዋል፡፡

መሳሪያዎቹም የጨረር፣ የሙቀት፣ የብርሃን፣ የብናኝ እና ትነት መጠንን መለካት የሚያስችሉ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፣ ከዚህ በፊት የነበረው የነበረው የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት ምልከታ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበርና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ ጥሩ መነሻ እንደሚሆንና ይህን ወደ ፊት ለማሳደግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

ከክልሎች የመጡና ድጋፎችን የተረከቡት የስራ ኃላፊዎች መሳሪዎቹ ዘመናዊ በመሆናቸው በሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመለካትና በማወቅ ጉዳቱን ለመከላከል እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

የተደረገዉን ድጋፍ የሰራተኛዉን ጤንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለዉ በመሆኑ ተደራሽነቱን በማስፋት ቀጣይነት ሊኖረዉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

መሳሪዎቹ ለአማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ኦሮሚያ ክልሎች፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ለፌዴራል መስሪያ ቤት ተበርክተዋል፡፡