የገዳ ሥርዓትን የሚያሳይ ሐውልት ተመረቀ

የገዳ ሥርዓትን የሚያሳይ ሐውልት በሰበታ ከተማ ዛሬ ተመርቋል፡፡

በሐውልቱ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት በኦዴፓ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት የከተማ አደረጃጀትና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሣሁን ጎፌ የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት ሲተዳደርበት የነበረው የገዳ ሥርዓት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

የሐውልቱ መመረቅ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከሚከበረው የኢሬቻ በዓል ጋር ሲገናኝ ትርጉሙ የጎላ እንደሆነ አቶ ካሣሁን አክለው ገልጸዋል፡፡

የገዳ ሥርዓት ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የኦሮሞ ሕዝብ እሴት ቢሆንም፣ የሐውልቱ መቆም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንድነት መገለጫ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው የሐውልቱን የግንባታ 8 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጪ የሰበታ ከተማ አስተዳድር መሸፈኑንና ሐውልቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሠላም ምልክት ነው ብለዋል፡፡

ለሐውልቱ ተጨማሪ እንክብካቤዎችና የማስዋብ ሥራዎች እንደሚከናወኑለትም ከንቲባው አክለው ገልጸዋል፡፡

ሐውልቱ ከአዲስ አበባ ቅርብ በሆነ ከተማ መቆሙ ለከተማዋም ሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራትና የመተሳሰብ ማሳያ ነው ሲሉ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ተወካዮች ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ለዘመናት የቀጠለውን የአባ ገዳዎች ሥርዓት በመጠበቅ ለኢትዮጵያዊያን በጋራና በሠላም መኖር ማሳያነቱን ማስጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡