የኢሬቻ በዓል በሆራ ፊንፊኔ ተከበረ

የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል በሆራ ፊንፊኔ በገዳ ሥርዓት መሰረት በአባ ገዳዎች ምርቃት ተጀምሮ በድምቀት ተከብሯል፡፡  

ከአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለበዓሉ በባህል አልባሳት ደምቀው ሆራ ፊንፊኔ ላይ የተገኙት የኦሮሞ እና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ተወላጆች ኢሬቻውን በአንድነት መንፈስ በጋራ አክብረውታል፡፡

በኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝቦች ላገኙት ፀጋና በረከት፣ ሰላምና ደስታ፣ ጤናና ዕድሜ፣ ፍቅርና ክብር፣ ብርሃንና ተሥፋ፣ ከአንድ ወቅት ወደ ሌላ ወቅት በአጠቃላይ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገራቸው አንድ አምላካቸው – ለዋቃ – ከመዲናዋ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የተሰባሰቡ ዜጎች በተለያዩ የኦሮሞ ባህላዊ ልብሶች ደምቀው በሆራ ፊንፊኔ ለፈጣሪያቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በርካታ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በዓሉ በሰላም እንዲከበር ጉልህ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው ታውቋል፡፡  

የገዳ ስርዓት በውስጡ ካቀፋቸው ክንዋኔዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከ150 ዓመት በኋላ ዘንድሮ ሲከበር የመጀመሪያው ነው።

በዓሉ በተለያዩ ቦታዎች የሚከበር ሲሆን፥ የኦሮሞ ህዝብ የማንነቱ መገለጫ የሆነውን በዓል በአንድ ላይ ተሰብስቦ በየዓመቱ የመስቀል/ጉባ/ በዓልን ተከትሎ ባለው የመጀመሪያ እሁድ ቢሾፍቱ በሚገኘው ሆረ አርሰዲ ያከብራል።

ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል፤ በበጋ ወቅት በከፍታ ቦታ ላይ የሚከበር ወይም ኢሬቻ ቱሉ እንዲሁም በጸዳይ ወቅት መግቢያ ላይ በወንዝ ዳር የሚከበረው ወይም ኢሬቻ መልካ በመባል የሚታወቅ ነው።