ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማስፈን እያደረገችው ያለው ጥረት ተደነቀ

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማስፈን እያደረገችው ያለውን ጥረት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር/ዩኤንኤችሲአር/ አደነቀ፡፡

ኮሚሽነሩ ሀገሪቱ በየጊዜው እያሻሻለች ባለው ፖሊሲዋ አማካኝነት ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍም አድንቋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ የተመራ ልዑክ በ70ኛው የድርጅቱ ከፍተኛ ኮሚሽነሮች ስራ አስፈፃሚ ጉባኤ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ አመራር በሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና በደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ሁኔታዎችን በማመቻቸት የተጫወቱት ሚናን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አዲሱ ቀብኔሳ ኢብሳ አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ940 ሺህ የሚልቁ ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ ያስታወሱት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን በመደገፍ ረገድ የሚታዩበት ክፍተቶችን መድፈን እንደሚገባም ነው የገለፁት፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የተሻለ ህይወትን ለመምራት የሚፈልጉ ዜጎችን በመደገፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል፡፡

ከመስከረም 26 እስከ 30፣ 2012 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጉባኤ ከ120 ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው ዘገባ ያመለክታል፡፡