ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

ጠቅላይ ሚኒስር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈዋል፡፡

በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሚዘጋጀው የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀደም ሲል ታይም መፅሄት ማስነበቡ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከሁለት አስርት አመታት ፍጥጫ እልባት በመስጠት፤ ሰላም በማምጣት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታትና ሌሎች ባመጧቸውም መሻሻሎች ሽልማቱን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ በእንግሊዝ የተለያዩ ፖለቲካዊ ትንበያዎችን በመስጠት የሚወራረደው ላድብሮክ 80% (4/1) ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምት ማስቀመጡም አይዘነጋም።

ዓመታዊው ሽልማት በአለም ውስጥ ለሰላም አስተዋፅኦ ያደረጉ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን እውቅና በመስጠት ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት የኮንጎ ዜግነት ያለው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጋና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ናዲያ ሙራድ ወሲባዊ ጥቃትን ለጦርነት መሳሪያነት መጠቀሚያነት ለማቆም በሰሩት ስራ አሸናፊ ሆነዋል።

በዚህ ዓመት ሽልማት 301 ዕጩዎች ያሉ ሲሆን፤ 223 ግለሰቦች እንዲሁም 78 ድርጅቶች መሆናቸውንም የኖቤል ተቋም አስታውቋል። ምንም እንኳን እነማን ዕጩዎች እንደሆኑ ባይታወቁም የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ግምቶቻቸውን እያስቀመጡ ቆይተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ በቀጠል የ16 ዓመቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ተንበርግና የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ግምትን ያገኙ ግለሰቦች ነበሩ፡፡