የአፍሪካ አገራት የህፃናትን መብት ለመጠበቅ የገቧቸዉን ስምምነቶች እንዲያከብሩ ተጠየቀ

በጦርነት ተጎጂ የሆኑ ህፃናትን መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሚመክረው ዉይይት ባለፉት 20 አመታት በጦርነት ምክንያት 5 ሚሊየን ህፃናት በሞቱባት አፍሪካ የህፃናት መብት እንዲከበርና ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ተጠይቋል፡፡

በዉይይት መድረኩ ከኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያና ኮንጎ የተገኙ ህፃናት ተሳትፈዋል፡፡
በዉይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሴቭ ዘ ችልድረን ዳይሬክተር ያ ቬል አገራት የህፃናትን መብት ለመጠበቅ የገቧቸዉን አለምአቀፍ ስምምነቶች ሊያከብሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ቶማስ ክዌሲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያገኙት የሰላም የኖቤል ሽልማት ለሰላም ያደረጉት ጥረት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዉ ለአህጉሩ ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የመሳሪያ ድምፅ እንዳይሰማ የተደረሰዉ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡
የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ዑመድ በበኩላቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን እየሰሩ መሆኑንና የኖቤል ሽልማቱም ይህን እንደሚያሳይ ተናገረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት በነበረዉ የዉስጥ መፈናቀል ችግር የደረሰባቸዉን ህፃናት መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡