400 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ

ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት በእስር ላይ የነበሩ 400 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል ።

በዛሬው እለት ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህርን አቋርጠው ሲጓዙ በሳዑዲ ዓረቢያ የፀጥታ ሀይል ተይዘው በእስር ላይ የቆዩ ናቸው ተብሏል።

ኢትዮጵያውያኑ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሃንስ ሾዴ ተገኝተው አቀባበል እንዳደረጉላቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የዛሬዎቹን ተመላሾች ጨምሮ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 3 ወራት 32 ሺህ 890 ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ  ተደርጓል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተል በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩና መሰል ችግር ያጋጠማቸውን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ፈቃድ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።