በመዲናዋ ከሚገኙ ወረዳዎች ግማሽ ያህሉ የዲጂታል መታወቂያ እየሰጡ ናቸው

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ወረዳዎች ግማሽ ያህሉ የዲጂታል መታወቂያ እየሰጡ መሆናቸውን የከተማው ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየው ለኢቲቪ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ካሉ 121 ወረዳዎች 62ቱ የዲጂታል መታወቂያ እየሰጡ ናቸው፡፡

አገልግሎቱ የሚሰጠው በቴሌኮም ኔትወርክ እገዛ እንደመሆኑ የዚህ መሰረተ ልማት ጥራትና ተደራሽነት ጉድለት የዲጂታል መታወቂያው በሁሉም የከተማዋ አስተዳደር እንዳይሰጥ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል አቶ ዮናስ፡፡

ከዚህ ባሻገር የሰው ሀይል እጥረት፣ ስራውን ማስፈጸሚያ በቂ ቢሮ ያለመኖር እና ለሰራተኞች የሚከፈል ደሞዝ አናሳ መሆኑ አገልግሎቱን በመዲናዋ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ችግር መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥረት የሚደረግ ሲሆን የኢንተርኔት ተደራሽነትና ጥራት መጓደል ለማከስተካከልም የሚመለከተው አካል ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሀላፊው ጠይቀዋል፡፡

አገልግሎቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 62 ወረዳዎች መስጠት ከተጀመረበት ሐምሌ 15 ጀምሮ 44 ሺህ ዲጂታል መታወቂያዎች ለህብረተሰቡ ተከፋፍሏል፡፡

አገልግሎቱ በዋናነት በቦሌ፣ ጉለሌ፣ ኮልፌ፣ ንፋስ ስልክ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በተሸላ ደረጃ እየተሰጠ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ ከአንድ በላይ ግላዊ ማንነትን ለመቀነስ ብሎም ተመሳስሎ የሚሰሩ ህገወጥ መታወቂያዎችን ለመከላከል እንዲሁም አጠቃላይ የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን ታስቦ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም በሁሉም ክፍለ ከተሞች መስጠት እንደሚጀመር መግለጹን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡