በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት የተገነባው ትምህርት ቤት ተመረቀ

በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት አማካኝነት የተገነባው የሎዛ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትበ ዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

በ20 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው ትምህርት ቤቱን በይፋ የከፈቱት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሲሆኑ የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፌደራል የትምህርት ዘርፍ አመራሮች እና ሌሎች እንግዶችም በምረቃው ላይ ተገኝተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ 28 የመማሪያ እና አራት የቤተ ሙከራ ክፍሎች፣ ቤተ መፃሕፍት እና የአስተዳደር ሕንጻ የተሟላለት ነው።

ትምህርት ቤቱ በአካባቢው የሚገኙ የአምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲሸጋገሩ በአቅራቢያቸው ለመማር ያስችላቸዋል ተብሏል።

በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳዳግ እንደሚረዳም ነው የተገለፀው፡፡

በቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት አማካኝነት በሀገሪቱ ከሚገነቡ 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አራቱ በአማራ ክልል ውስጥ በጎንደር፣ ደባርቅ፣ ዋግ ኽምራ እና ደቡብ ወሎ ዞን እንደሚገነቡ ታውቋል።

ምንጭ፦ኢቢሲ