የሕግ መረጃን ማግኘት አዳጋች መሆኑን ጥናት አመለከተ

የሕግ ጽሑፎችን ወይም የሕግን መረጃን ማግኘት አዳጋች መሆኑን የፍትህና የሕግ ምርምር ስልጠና ኢንስቲትዩት ያካሄደው ጥናት አመለከተ፡፡
ኢንስቲትዩቱ በ2011 በጀት ዓመት የሕግ ጽሑፎችን ወይም የሕግን መረጃ ማግኘት በተመለከተ ባደረገው ጥናት ችግሩን መሻገር እንዳልተቻለ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያከናወነው ባለው የምክክር መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የህግ ተመራማሪ ወ/ሮ የትናየት ደሳለኝ ጥናቱን ሲያቀርቡ እንደገለፁት ጥናቱ በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች፣ የፖሊስ ኮሚሽን ፍርድ ቤቶችና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንደተከናወነና በቀጣይም ችግሮቹን ለመቅረፍና የመንግስት ፖሊሲን ለመደገፍ ያስችላል፡፡
ሕግና ሕግ ነክ መረጃዎች ያላቸውን ልዩ ባሕሪይ ታሳቢ ያደረገ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ አማራጭ የመረጃ መስጫ መንገዶች በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ አለመሆን፣ መረጃ ማግኘት በግለሰቦች መልካም ፈቃድኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች አለመኖራቸው እና የግንዛቤ እጥረት ለችግሩ መባባስ ጥናቱ የለያቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡
በፍትህ ተቋማት የሚገኙ ቤተመጽሐፍት ከሌሎች የሕዝብ ቤተመጽሐፍት ጋር በመስራት ሕግና የሕግ መጽሐፍተን ተደራሽ ማድረግ፣ መረጃ መስጫ ሱቆችን መክፈት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሕብረተሰቡ በስፋት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚሉት ደግሞ ጥናቱ በመፍትሔነት ያስቀመጣቸው ሐሳቦች እንደሆኑ ወ/ሮ የትናየት አመልክተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ “የእርሻ መሬት ይዞታና የማስተላለፍ መብት” በሚለው የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዜጎች ባላቸው የመሬት ይዞታ ዋስትና ተገቢውን የሕግ ከለላ አለማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ደቡብ ሕዝቦች፣ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልሎች በተደረገው ጥናት ወደ ፍርድ ቤት ከሚመጡ የፍትሃብሄር ጉዳች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት የእርሻ መሬት ይዞታን የሚመለከቱ ስመሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በሕገመንስግሰቱ አንቀፅ 40 ንዑስ ቁጥር 4 ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘት መብት ብቻ ሳይሆን ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው ሲል ቢደነገግም ይህ መብታቸው ግን እምብዛም ሲከበር አይታይም ተብሏል፡፡
የአርሶ አደሩ የእርሻ መሬት በህግ ከተቀመጠው ውጪ በባህልና በተለምዶ ማስተላለፍ፣ ከህግ ውጪ ያሉ አሰራሮችና ክፍተቶች መበራከት፣ የተደራጀ የእርሻ መሬት አያያዝ ሥርዓት አለመዘርጋት፣ ህጎች መብትን የሚሰጡት ለክልሎች ነዋሪዎች በመሆኑ የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራት መብት የገደቡ መሆናቸው በጥናቱ የተመለከቱ ችግሮች ናቸው፡፡
ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የገጠር መሬት ጉዳይን ሊዳኝ የሚችል ራሱን የቻለ ተቋም መፍጠር፣ ለልማት ለሚነሱ አርሶአደሮችን የሚሰጣቸውን የገንዘብ ካሳ ተለዋጭ ቦታ በመስጠት ቢሆን እና ከገጠር መሬት ጋር ያለ መረጃ የተደራጀና በቴክኖሎጂ የታገዘ ቢሆን የሚሉት ደግሞ ጥናቱ በመፍትሄ ሐሳብነት ያመላከታቸው መሆኑን በምክከር መድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡