ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከዓመታት የሻከረ ግንኙነት በኋላ አሁን መለሳለስ እያሳዩ መምጣታቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይገልጻሉ ፡፡
በአፍካ ህብረት እና በጎረቤታቸው ኢትዮጵያ ድጋፍ ነው አገራቱ ሻክሮ የነበረውን ግንኙነትና ወንድማማችነት እንዲያንሰራራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከር የጀመሩት ።
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የራሳቸውን መንግስት ከመሠረቱ ማግስት ጀምሮ በየእለቱ በድንበሮቻቸው አካባቢ የሰው ህይወት ይጠፋል፡፡ በርካቶችም ቀዬያቸውን ጥለው ተሰደዋል ፡፡
ይህንኑ ለመፍታት በርካታ አገራት እና መንግስታት እንዲሁም ግለሰቦች ብዙ ጥረር ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይታወቃል ።
ኪር እና አል በሽር የጋራ አጀንዳዎቻቸውን ለመቅረፅ በዝግጅት ላይ እንዳሉ የመረጃ ምንጮች ያመላክታሉ ፡፡
እነዚህ ድንበርተኞች በድንበሮቻቸው አካባቢ ስለሚኖረው ሰላምና መረጋጋት፣ ስለዜጎቻቸው ደህንነት እና ስለ ዘላቂ እድገታቸው ለመምከር መሰናዷቸውን አጠናቀዋል ሲል ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡
የሀገራቱ ዲፕሎማቶች እና የፕሬዝደንቶቹ አማካሪዎች ለዜና ምንጩ እንደተናገሩት፤ የውጭ ጉዳይ፣ የደህንነት፣ የውስጥ ጉዳይ፣ መከላከያ ኃይል እና የፍትህ ሚኒስትሮቻቸው የቅድመ መሰናዶ ውይይት አካሂደው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
መንግስታቱ የስምምነት ፊርማዎቻቸውን የሚያሳርፉባቸውን አበይት ርዕሶችንም መርጠው አርቅቀዋል፡፡
ሆኖም የተነሱት ጉዳዮች እና የሚስማሙባቸው ነጥቦች እንዲሁም የፕሬዝደንቶቹ የግንኙነት ቀን ተለይቶ አልታወቀም ብሏል ሱዳን ትሪቡን፡፡
የቅድመ መሰናዶ የድርድር ኮሚቴዎች ከሁለቱም ወገኖች በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ የተመረጡ እና በሚፈለገው መንገድ የተወያዩ እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡
ውይይታቸውንም እንደ ከዚህ ቀደሙ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
አሁን ሳልቫ ኪር እና አል በሽር የሚኖራቸው ውይይት ሁለቱ ሱዳኖች በ2012 የተፈራረሙትን የደህንነት ጥምረት ስምምነት በተሻለ ደረጃ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አገራቱ እስካሁን ድረስ ህጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ለታጠቁ ኃይሎች የሚያደርጉትን ያልተገባ ድጋፍ ለማቆም ስምምነት ላይም ይደርሳሉ ተብሏል፡፡( ምንጭ: ሱዳን ትሪቡን)