ሱዳንና ቻይና ነዳጅ በጋራ ሊያወጡ ነው

ሱዳን እና ቻይና በመጪዎቹ ጊዚያት የነዳጅ ሀብት ማበልፀግ ስራ በጋራ ለመስራት የሚያበቃቸውን ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በመሆኑም በነዳጅ ፍለጋ ዙርያ ያተኮረው ድርድርም በቻይና ነዳጅ አውጪ ኩባንያዎችና በሱዳን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር በኩል መጀመሩ ታውቋል፡፡

ድርድሩም በጠቃሚ ስምምነቶች መቋጫ እንደሚያገኝ የገለፁት በቤጂንግ የሱዳን አምባሳደር የሆኑት ሻዊር ሰድ ናቸው፡፡

ቻይና የሱዳን ቀዳሚ ስትራቴጂካዊ አጋር ስትሆን በነዳጅና የተፈጥሮ ሀብት መበልፀግ ከፍተኛ ተሳትፎ ታደርጋለች፡፡

የቻይናው ብሄራዊ የፔትሮሌም ኮርፖሬሽንም በምዕራብ ሱዳን ነዳጅ ማፈላለግና የማጣራት ተሳትፎ ማድረጉ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

በቤጂንግ በተደረገው ድርድር ልኡካኖችን የመሩት አምባሳደሩ በማጠናቀቅያው ላይ የሚስማሙበት ውል ካርቱም ያላትን የነዳጅና የተፈጥሮ ሀብት ለምጣኔ ሀብታዊ እድገቷ ጉልህ ድርሻ ሊያበረክት እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

ቻይና ኩባኒያዎቿ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይና ውጪ የነዳጅ ማጣራት ስራ የጀመሩት በሱዳን መሆኑን ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነትንም ያተረፈችበት በመሆኑ ትልቅ እውቅና አላት፡፡

ምንም እንኳን ቤጂንግ ካርቱም ባለባት የብድር እዳ ቅሬታ ብታሰማም በነዳጅ ማበልፀግ ረገድ በስምምነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በቻይና ኩባኒያዎች አማክይነትም ሱዳን በቀን አስከ 120 ሺ በርሜል ነዳጅ ታምርታለች፡፡ (ሱዳን ትሪቡን)