ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በጅቡቲ እየተካሄደ ነው

ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት 2ኛው ዓለም አቀፍ የጅቡቲ የንግድ ትርዒት ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ዓለም አቀፍ የንግድት ትርኢቱንም የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኡማር ጊሌህ በይፋ መርቀው ከፍተውታል።  

ፕሬዚዳንት እስማኤል ኡማር ጊሌህ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርም ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቱ በጅቡቲ ያለውን ምቹ የገበያ አማራጭ ለማሳየት ያግዛል ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም ሆነ ዓለም አቀፉ የንግድ ማህበረሰብ በሀገሪቱ የሚገኘውን የንግድ አማራጮች እንዲጠቀሙም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም የሀገሪቱ መንግስት ለግሉን ዘርፍ እድገት በትኩረት ይሰራል ያሉ ሲሆን፥ ለዘርፉ ማደግም ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በጅቡቲ የኢፌዴሪ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ በበኩላቸው የንግድ ትርኢቱ በተለይም ለኢትዮጵያውያን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

በንግድ ትርኢቱ ላይ ከተሳተፉ ሀገራትም ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ እና ከጂቡቲ ጋር በመሠረተ ልማት የተሳሰሩ በመሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቱ ላይ ከ11 በላይ ኢትዮጵያ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ የቆዳ ምርቶች፣ የሀገር ባህል አልባሳት፣ የባልትና ውጤቶች፣ ቡና፣ ጥራጥሬና ቅመም ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል።(ኤፍቢሲ)