ታንዛኒያ በዊግና ሰው ሰራሽ ጸጉር ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ጣለች

የታንዛኒያ መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ሲል ከውጪ በሚገባ ሰውሰራሽ ጸጉርና ዊጎች ላይ 25 በመቶ እንዲሁም ሀገር ውስጥ በሚመረቱት ላይ ደግሞ 10 በመቶ ቀረጥ ጥሏል።

የሃገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ፊሊፕ ምፓንጎ ወሳኔውን ያሳወቁት ሐሙስ እለት ዓመታዊ የበጀት እቅዳቸውን ይፋ ባደረጉበት ጊዜ ሲሆን ከቀጣዩ ሐምሌ ወር ጀምሮም ተግባራዊ ይሆናል።

ከውጪ የሚመጡት ዊጎችን በታንዛኒያ የሚገኙ ሴቶች አዘውትረው የሚጠቀሙበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ርካሹ ዊግ አራት ዶላር ሲያወጣ ከፍተኛው ደግሞ እስከ 130 ዶላር ይሸጣል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ እንዲሆን የተደረገበትን ውሳኔ በማንሳት ታክሱ እንዲከፈል እንደሚደረግ አሳውቀዋል።

ለዚህም ሚኒስትሩ እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ነጋዴዎች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያውን አሁንም ድረስ እየሸጡ ያሉት የተጨማሪ እሴት ታክሱ ከመነሳቱ በፊት ባለው ዋጋ በመሆኑ ለተጠቃሚዎች ምንም አይነት ለውጥ ስላላመጣ ነው ብለዋል።

እነዚህ ታንዛኒያዊ ሴቶችን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ይፋ ከተደረጉ በኋላ በርካታ ሴቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መንግሥት ሴቶችን ለመቅጣት የወሰደው እርምጃ ነው በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የቀረጥ ጭማሪ ከተደረገባቸው ነገሮች መካከል ቀደም ሲል 25 በመቶ የነበረው ቸኮሌት ላይ ተጥሎ የቆየው ቀረጥ ወደ 35 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።